የአባላዘር በሽታ (ምንነት፣ መንስኤ፣ ምልክት እና ሕክምና)

  • “የአባላዘር በሽታ ሕመምተኞች ሰው ሁልጊዜ ምልክቶች ይኖራቸዋል።”
  • “ብዙ የፍቅር ጎደኛ የአላቸው ሰዎች ብቻ ናቸው በአባላዘር በሽታ የሚጠቁት።”
  • “ኮንዶም መጠቀም የአባላዘር በሽታን ሙሉ በሙሉ ይከላከላል፡፡”

ከላይ የተዘረዘሩትን ጨምሮ ስንቶቻችን ነን ስለአባላዘር በሽታ የተሳሳቱ ሐሳቦችን ሰምተን የምናውቀው?

በዚህ ጽሑፍ ስለአባላዘር በሽታ ምንነት፣ መንስኤ፣ ምልክቶች እና የሕክምና አማራጮችን በዝርዝር እናያለን።

የአባላዘር በሽታ ምንነት

በግብረ ስጋ ግንኙነት ጊዜ ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፉ በሽታዎች የአባላዘር በሽታዎች ብለን በወል ስም እንጠራቸዋለን። ከነዚህም ውስጥ በስፋት የሚታወቁት ጨብጥ፣ ቂጥኝ እና የኤች አይ ቪ በሽታ ይጠቀሳሉ። ከዚህ በተጨማሪ ይህ በሽታ ከእናት ወደ ልጅ በእርግዝና ወይም በወሊድ ወቅት ሊተላልፍ ይችላል። ይህ በሽታ የሚከሰተው በተለያዩ የባክቴሪያ፣ የቫይረስ እና የፓራሳይት አይነቶች ሲሆን እነዚህ በሽታ አምጪ ተህዋስያን በግኑኝነት ወቅት ከሰው ወደ ሰው ይተላለፋሉ። በአማካኝ በየቀኑ ወደ 1.4 ሚሊየን የሚጠጉ ሰዎች በዚህ በሽታ እንደሚጠቁ ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡

ምንም እንኳን  ኮንዶም መጠቀም የበሽታውን ስርጭት ለመቀነስ ቢረዳም እንደ HPV ያሉ የአባላዘር በሽታ የሚያስከትሉ ቫይረሶችን አይከላከልልንም።

የአባላዘር በሽታ ምልክቶች

አብዛኛውን ጊዜ በዚህ በሽታ የተጠቁ ሰዎች ምልክቶችን ላያሳዩ ይችላሉ። ነገር ግን ምልክቶች ከአሏቸው ከስር ከተዘረዘሩት ውስጥ አንድ እና ከአንድ በላይ ሊኖራቸው ይችላል።  

ለምሳሌ

  • ከብልት የሚወጣ ያልተለመደ ሽታ ያለው ፈሳሽ
  • ብልት አካባቢ የሚወጣ ጥቃቅን ፈሳሽ ያለው እብጠት
  • በብልት ዙሪያ ብሽሽት አካባቢ የሚታይ እብጠት
  • የማሳከክ ስሜት
  • ሽንት ስንሸና ማቃጠል
  • በግንኙነት ጊዜ የሚኖር ሕመም

ከላይ የተጠቀሱ ምልክቶችን ካዩ ከፍቅረኛዎ ወይም ከትዳር አጋርዎ ጋር በመሆን መመርመር ያስፈልጋል።

የአባላዘር በሽታ ምርመራ

ከላይ የተጠቀሱትን ምልክቶች አይተው ወደ ሐኪም ቤት ከሄዱ በኃላ ሐኪሙ የተለያዩ አካላዊ ምርመራዎችን ያደርግልዎታል። የአባላዘር በሽታ ሕክምና ከሌላው በሽታ ሕክምና የሚለየው ሕመምተኛው ከሚያሳያቸው ምልክቶች እና አካላዊ ምርመራ በመነሳት መድኃኒቱ የሚታዘዘው። ስለዚህ ለመታከም ሲሄዱ ያለምንም መሳቀቅ ሕመምዎትን መግለፅ አስፈላጊ ነው።

ከአባላዘር በሽታ ጋር ተያይዘው የሚመጡ ችግሮች

ይህ በሽታ ካልታከመ ከስር የተዘረዘሩትን የጤና ችግሮች ሊያስከትል ይችላል።

  • መካንነት
  • የኤ.ች.አ.ይ.ቪ በሽታ ተቃላጭነትን ይጨምራል
  • ወደ ካንሰር መቀየር
  • እንዲሁም ወደ ሰውነት የተሰራጨ ኢንፌክሽን ሊኖር ይችላል።

የአባላዘር በሽታ ሕክምና

በዋነኝነት ይህ በሽታ የሚታከመው በፀረ ተህዋስያን መድኃኒቱ ነው። ይህም እንደ በሽታው ዓይነት ይለያያል።

ከአባላዘር በሽታ እንዴት እራሳችንን መጠበቅ እንችላለን?

የበሽታው ዋነኛ መተላለፊያ መንገድ የግብረስጋ ግኑኙነት እንደመሆኑ መጠን ከተቻለ መቆጠብ ካልሆነ ደግሞ ከአንድ አጋር ጋር መወሰን ያስፈልጋል። በተጨማሪም በሽታው ምልክት ላያሳይ ስለሚችል ራሳችንንም ሆነ የፍቅር አጋራችንን ከበሽታው ለመጠበቅ መመርመር እና ተገቢውን ሕክምና ማግኘት አስፈላጊ ነው። እንዲሁም ነፍሰጡር እናቶች በሽታውን ወደ ልጃቸው ሊያስተላልፉ ስለሚችሉ በእርግዝና ወቅት ምርመራ ማድረግ ያስፈልጋል።

ስለ አባላዘር በሽታ በቂ መረጃ እንዳገኙ ተስፋ እናረጋለን። መልካም ቀን።

ተጨማሪ ጽሑፎች

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top