15 የደም ግፊት በሽታ መንሥኤዎች ከነማብራሪያቸው

አንድ ሰው የደም ግፊት በሽታ አለበት የሚባለው የላይኛው ልኬት 130 እና ከዛ በላይ ከሆነ እንዲሁም የታችኛው ልኬት 80 እና ከዛ በላይ ከሆነ ነው። ይህም በአምስት ዋና ዋና ክፍሎች ይከፈላል።

  • ትክክለኛ የግፊት መጠን የሚባለው: ከ 120 በ 80 (120/80) በታች ሲሆን ነው።
  • በመጠኑ ከፍ ያለ ነገር ግን የበሽታ ደረጃ ላይ ያልደረሰ የደም ግፊት የሚባለው ደግሞ: የላይኛው በ120 እና 129 መካከል ከሆነ ወይም የታችኛው ልኬት ከ 80 በላይ ከሆነ ነው።
  • የመጀመሪያ ደረጃ የደም ግፊት የምንለው የላይኛውበ 130 እና 139 መካከል ወይም   የታችኛው ልኬት በ 80 እና 89 መካከል ከሆነ ነው።
  • ሁለተኛ ደረጃ የደም ግፊት የምንለው የላይኛው ከ 140 በላይ ወይም የታችኛው ከ 90 በላይ ከሆነ ነው።
  • በጣም ከፍተኛ የደም ግፊት (Hypertension crisis) የሚባለው ደግሞ የላይኛው ልኬት ከ 180 በላይ ከሆነ ወይም የታችኛው ልኬት ከ 120 በላይ ከሆነ ነው። በቤትዎ ሆነው ግፊትዎትን ሲለኩ ይሆን ወጤት ካገኙ በፍጥነት ወደ ሆስፒታል መሄድ ያስፈልጋል።

የደም ግፊት ከአለባቸው ሰዎች ውስጥ ከ 80 አስከ 95 በመቶ የሚሆኑት ላይ ምክንያቱ የማይታወቅ ሲሆን ይህም የደም ግፊት አይነት ኢሴንሽያል ይባላል። የተቀሩት በሽተኞች ግን የደም ግፊታቸው መንሥኤ የታወቀ ነው። ከነዚህ የደም ግፊት በሽታ መንሥኤዎች ውስጥ ዋና ዋናዎቹ በዚህ ቪዲዮ ላይ ተብራርተዋል፤ ይከታተሉን።

የኩላሊት ደም ወሳጅ መጥበብ (ወይም የኩላሊት ደም ግፊት)

ወደ ኩላሊት ደም የሚወስደው የደም ስር በተለያዩ ምክንያቶች አማካኝነት ሊጠብ ይችላል። በዋነኝነት እድሜያቸው የገፋ ሰዎች ላይ የደም ቧንቧቸው በስብ ሊሞላ ይችላል። ይህም የደም ስር ድረቀት ያስከትላል። በዚህ ምክንያት የኩላሊት የደም ወሳጅ ከጠበበ እና ወደ ኩላሊት የሚሄደው ደም ካነሰ ኩላሊት ሬኒን የሚባል ኬሚካል ታመነጫለች። ይህም በአጠቃላይ ሰውነታችን ውስጥ ያሉ የደም ቧንቧዎች እንዲጠቡ እና የደም ግፊት በሽታ እንዲፈጠር መንሥኤ ይሆናል።

ሌሎች የኩላሊት በሽታዎች

ኩላሊት ደምን የማጣራት አቅሟን የሚቀንሱ የተለያዩ በሽታዎች የደም ግፊት እንዲፈጠር ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ።

በቀላሉ ልንከላከላቸው የምንችላቸው የኩላሊት በሽታ ምልክቶችን ለማወቅ ሊንኩን ይጫኑ።

የኩላሊት በሽታን እንዴት መከላከል እንደምንችል ለማወቅ ሊንኩን ይጫኑ።

ከደም ቧንቧ ጋር የተያያዙ የአፈጣጠር ችግሮች ለምሳሌ ኮአርክቴሽን ኦፍ አኦርታ (Coarctation of Aorta)

ይህ በሽታ በህፃናት ላይ የሚታይ የአፈጣጠር ችግር ሲሆን ከወገብ በታች ያለው የሰውነት ክፍል ትንሽ ደም አግኝቶ የላይኛው የሰውነት ክፍል ደግሞ ከፍተኛ ደም ሲያገኝ ነው። የዚህም ምክንያቱ ልብ የምትረጨው ደም በዋነኝነት የሚሄደው ወደላይኛው የሰውነት ክፍል በመሆኑ ነው። ሰውነታችንም ይህም ለማመጣጠር ያለው አማራጭ የደም ግፊት መጨመር ሲሆን ይህም የደም ግፊት ያስከትላል። ለህልፈትም ሊዳርግ ይችላል።

የአድሬናሊን እጢ (ለምሳሌ ፊዬክሮሞሳይቶማ / Pheochromocytoma )

ፊዬክሮሞሳይቶማ በወጣቶች እና በጎልማሶች ላይ በብዛት የሚገኝ እጢ ሲሆን እነዚህ ህመምተኞች የደም ግፊትን የሚጨምሩ ካቲኮላማይን የሚባሉ ሆርሞኖችን በብዛት ያመነጫሉ። ይህም ከደም ግፊት መጨመር በተጨማሪ ድንገተኛ የሆነ የራስ ምታት፣ የልብ ምት መፍጠን፣ ከፍተኛ ላብ ያስከትላል። በተጨማሪም የክብደት መቀነስ እና የስኳር በሽታ ሊያስከትሉ ይችላሉ። ይህ በሽታ በደም፣ በሽንት እና በ ራጅ ምርመራ ይታወቃል።

ከፊዬክሮሞሳይቶማ ውጪ ሊሎች የደም ግፊትን የሚያስከትሉ የአድሬናሊን እጢ አይነቶች አሉ። እነዚህም እጢዎች አልዶስትሮን የሚባል ሆርሞን በማመንጨት የደም ግፊት እንዲጭምር ምክንያት ይሆናሉ።

የአተነፋፈስ ችግር (ወይም sleep apnea )

በዚህ በሽታ የሚሰቃዩ ሰዎች በሚተኙበት ጊዜ የአየር ቧንቧቸው በተለያዩ ምክንያቶች ስለሚጠብ ለመተንፈስ ይቸገራሉ፤ ያንኮራፋሉ፤ እንቅልፋቸው ይቆራረጣል። ይህም በደም ውስጥ ያለው የኦክስጂን መጠን ስለሚቀንስ ሰውነታችን እሱን ለማካካስ በልብ ላይ ስራ ያበዛል። እንዲሁም የደም ግፊት እንዲጨምር ምክንያት ይሆናል።

ከዚህ በተጨማሪ እንደአጠቃላይ ለደም ግፊት በሽታ አጋላጭ የሆኑ ነገሮች አሉ። ለምሳሌ

  • ሲጋራ ማጨስ
  • የአልኮል ሱስ
  • ጭንቀት
  • ከመጠን ያለፈ የክብደት መጨመር
  • የእንቅስቃሴ እጥረት
  • ጨው የበዛበት ምግብ በብዛት መመገብ
  • የሆርሞን ይዘት ያላቸው የወሊድ መቆጣጠሪያ እንክብሎችን መጠቀም
  • የእንቅርት ሆርሞን ጋር ተያይዘው የሚመጡ ችግሮች
  • ከፍተኛ የኮሪትሶል ሆርሞን መመረት (ወይም በኢንግሊዘኛው ኩሺንግ ሲንድረም ይሉታል) እንዲሁም
  • የእድሜ መግፋት በተፈጥሮ የሰው ልጅ እድሜው በጨመረ ቁጥር የደም ቧንቧ ግርግዳ እየደረቀ እና ብዙ ስብ እየተከማቸበት ስለሚመጣ ግፊቱም በዛው ልክ እየጨመረ ይመጣል። እንዲሁም
  • ከቤተሰብ የሚወረስ ወይም የደም ግፊት ያለበት የቤተሰብ አባል መኖር ለደም ግፊት በሽታ ያጋልጣሉ።

ለበለጠ መረጃ ከስር ያለውን ቪዲዮ ይመልከቱ

በሚቀጥለው ስለ ደም ግፊት ምልክቶች እናያለን፤ ስላዳመጣችሁን እናመሰግናለን። ተመሳሳይ የጤና ምክሮችን ለማግኘት ብሎጋችንን እና የዩትዮብ ቻናላችንን ሰብስክራይብ በማድረግ ቤተሰብ ይሁኑ።

1 thought on “15 የደም ግፊት በሽታ መንሥኤዎች ከነማብራሪያቸው”

  1. Pingback: ጭንቀት በጤና ላይ የሚያስከትለው ጉዳት ምንድነው? እንዴትስ ማስወገድ ይቻላል?

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top