የ ጭንቀት ቀጥተኛ ፍቺው በተፈጠረ ወይም ሊፈጠር በሚችል የህይወት አስቸጋሪ ሁኔታ ምክንያት የሚሰማን አሉታዊ የሆነ የስሜት መረበሽ ነው። ይህም የስሜት መረበሽ ማንኛውም ሰው ላይ ሊፈጠር የሚችል ሲሆን ከሰራንበት እንደ ጠቃሚ ተጽዕኖ በተቃራኒው ደግሞ ካልሰራንበት ደግሞ አዕምሮ እና ጤናችን ላይ አሉታዊ ጫና የሚፈጠር ስሜት ነው።
ይህን ፁሁፍ ለመፃፍ በዋነኝነት የተጠቀምኩት ከ 6 ሚሊዮን ኮፒ በላይ የተሸጠው እና በ Dale Carnegie የተፃፈው How to Stop Worrying and Start Living በሚለውን መጽሀፍ ላይ የተገለፀውን ጭንቀትን ለማስወገድ የሚረዱ ዘዴዎችን ነው።
ይህ ትምህርታዊ ፁሁፍ ተዘጋጅቶ የቀረበው ጊቭ ሶሳይቲ ኢትዮጵያ ከሚባል በጎ አድራጎት ድርጀት ጋር በመተባበር ነው። ጊቭ ሶሳይቲ ኢትዮጵያ ባለፉት 8 ወራት ብቻ ከ 200 በላይ በጎ ፍቃደኛ ጤና ባለሙያዎችን በማስተባበር ከ 1300 በላይ ለሆኑ ህመምተኞች ነፃ የህክማና እርዳታ ሰጥተዋል። ይህን በጎ አድራጎት ድርጅት በቀጥታ ለማግኘት ከፈለጉ አድራሻቸውን ከስር ዲስክሪብሽኑ ላይ አስቀምጠናል።
ጭንቀት በሰውነታችን ላይ የሚያደርሰውን ጫና ምንድነው?
እንደሚታወቀው ጭንቀት እንደ ድባቴ እና ከእንቅልፍ ጋር ተያይዘው የሚመጡ ችግሮችን ከማስከተሉም በላይ በሽታን የመከላከል አቅም ይቀንሳል። እንዲሁም የራስ ምታት፣ የጀርባ እና የመገጣጠሚያ ሕመም እንደሚያመጣ በሳይንስ ተረጋግጧል።
በተጨማሪም ከፍተኛ የሆነ ጭንቀት የአስም ሕመም እንዲነሳ ሊያደርግ ይችላል። እንዲሁም ለደም ግፊት፣ ለልብ ድካም እና ለስኳር በሽታ ያጋልጣል።
በተደረገው ጥናት መሰረት 43 በመቶ የሚሆነው ወጣት ከጭንቀት ጋር በተያያዘ የጤና እክል ያጋጥመዋል። እንዲሁም ወደ ሆስፒታል ከሚመጣው ሕመምተኛ ውስጥ እስከ 80 በመቶ የሚሆነው ከ ጭንቀት ጋር የተያያዘ የጤና እክል ይኖራቸዋል።
ከዚህ በተጨማሪ ጭንቀት የምግብ ፍላጎት መቀነስ፣ የሆድ መነፋት እና ምቾት ማጣት እንዲፈጠር ያደርጋል። ከዚህ ጋር ተያይዞም ተቅማጥ እና ትውከት ሊያስከትል ይችላል።
በሌላ በኩል ጭንቀት የወሲብ ስሜትን ይቀንሳል እንዲሁም ስንፈተ ወሲብ እና መሃንነትን ያስከትላል። በወጣት ሴቶች ላይ ደግሞ የወር አበባ መዛባት እና ህመም ያለው የወር አበባ ኡደት እንዲኖር ያደርጋል።
ታዲያ ጭንቀት ይሄን ያህል አሉታዊ ጫና ካለው፣ እንዴት መከላከል እንደምንችል ማውቅ እና መተግበር እጅግ አስፈላጊ መሆኑን መረዳት ያሻል።
ጭንቀትን እንዴት ማስወገድ ይችላል?
በመጽሀፉ ላይ የተገለፀው ጭንቀትን ለማስወገድ የሚረዳ የመጀመሪያው ደረጃ ያሉበትን አስቸጋሪ ሁኔታ በመመርመር የከፋ የምንለውን ውጤቶች በዝርዝር መፃፍ፤ በመቀጠልም ይህ ሁኔታ ውስጥ ብንገባ ምን ማድረግ እንዳለብን አማራጭ ማስቀመጥ። ይህም ሁኔታውን በሙሉ ልብ መቀበል እንደምንችል ያግዘናል።
ለምሳሌ ከቀናት በኃላ ህይወትዎን የሚለውጥ ስራ ለመቀጠር ቃለመጠይቅ አለዎት እንበል። ይህን ቃለመጠይቅ ላይ ምን ለብሰው እንደሚሄዱ እና በምን መልኩ ጥያቄዎችን መመለስ እንዳለብዎ በማሰብ ተጨንቀዋል።
እስኪ ቁጭ ብለው ይሄን ቃለመጠይቅ ባያልፉ ምን እንደሚፈጠር አስቡ። ቢበዛ አሁን ያሉበት ስራ ላይ ይቆያሉ። ወይም በትንሽ ካፒታል የራስዎን ነገር ይጀምራሉ። ያም ካልሆነ የማስተርስ ትምህርትዎን ይቀጥላሉ። ወይም ሌላ የክህሎት ስልጠና ይወስዳሉ።
ቃለመጠይቁን ባያልፉ የሚያደርጉትን ነገሮች መዘርዘሩ 2 ጥቅሞች አሉት።
- ይህን ስራ ባያገኙ የአለም መጨረሻ እንዳልሆነ ይረዳሉ።
- ሌላ ብዙ አማራጮች እንዳለዎት ሲያውቁ ደግሞ ለቃለ መጠይቁ የሚሰጡት የተጋነነ ግምት ይቀንሳል። ይህም ጭንቀትዎን ይቀንሳል፤ በራስ መተማመንዎን ይጨምራል። ይህ ደግሞ ቃለመጠየቁን በብቃት እንዲወጡ ይረዳዎታል።
በራሴ ህይወት ያጋጠመኝን ላካፍላችሁ።
በሕክምና ትምህርት ከፍተኛ ቦታ የሚሰጠው ኳሊፊኬሽን የሚባል ፈተና አለ። አንድ ሐኪም ሐኪም ተብሎ እንዲጠራ ይህን ፈተና ማለፍ አለበት። ለዚህ ፈተና ለመዘጋጀት በትንሹ ላለፉት 2 አመታት የተማርነውን ማጥናት ይኖርብኛል። ያለኝ ጊዜ ደግሞ አንድ ወር ብቻ ነው።
በመጀመሪያው 4 ቀናት አንድም ርዕስ አንብቤ መጨረስ አልቻልኩም። ምክንያቱም ቶፒኩን ከቨር አላረገውም የሚል ከመጠን ያለፈ ጭንቀት ስለነበረኝ ነው። በዚህ ሁኔታ ለአንድ ሳምንት ከቆየው በኃላ ፈተኛውን በወድቅ ምን እንደምሆን ቁጭ ብዬ አሰብኩበት።
ከ 3 ወር እስከ 1 አመት እደግማለሁ። እንደውም ትምህርቱን ለሁለተኛ ጊዜ መማሬ በትክክል አንብቤ እና ተረድቼ እንዳልፍ ያደርገኛል። በዛ ላይ ከግቢ ተመርቆም ወቶ ስራ የማያገኝ ስንት ሰው አለ። አንድ አመት ቁጭ ብሎ የሚያባክን። እኔ እየተማርኩ ባሳልፈው ይጠቅመኛል እንጂ አይጎዳኝም።
እነዚህን ሐሳቦች ባሰብኩ ቁጥር ለዚህ ፈተና የሰጠሁት የተጋነነ ግምት እየቀነሰ መጣ። ይሄን ፈተና መውደቅ የአለም መጨረሻ አለመሆኑ ተገለጠልኝ። ከዚህ ጋር ተያይዞም አላስጠና ያለኝ ጭንቀት ቀነሰ።
ስለዚህ ፈተናው እስከሚደርስ ተረጋግቼ ማጥናት ጀመርኩ። ካሰብኩት በላይ ብዙ ቶፒክ ከቨር አድረጌ በጥሩ ውጤት አለፍኩ።
እስኪ እርስዎም የሚያስጨንቅዎትን ነገር ዘርዝረው ያስቀምጡ። ስራ ማጣት ነው? ወይስ ትምህርት ነው? ወይስ የቤተሰብ ጉዳይ ነው? ሊፈጠር የሚችለውን የከፋ ውጤት ለይተው ይፃፉ ፤ በመቀጠልም ይህ ሁኔታ ውስጥ ቢገቡ ምን ማድረግ እንዳለብዎ አማራጭ ያስቀምጡ። ሊፈጠር የሚችለውን የከፋ ሁኔታ ሙሉ በሙሉ ከተቀበሉት በኃላ ተረጋግተው ምን ማድረግ እንዳለብዎ ያስቡ። ጭንቀትዎ ስለሚቀንስ እና በራስ መተማመንዎ ስለሚጨምር የተሻል አማራጭ ማስቀመጥም ሆነ ወስነው ወደ ስራ መግባት ይቀልዎታል።
አማራጭዎን ዘርዝረው ካስቀመጡ በኃላ ወደ ስራ ሲገቡ መተግበር ያለብዎ ሁለተኛው ደረጃ ዛሬ ላይ ማድረግ ስላለብን ነገር ብቻ ማሰብ ነው። ፀሃፊው ከዚህ ጋር አያይዞ አንድ ታሪክ ያነሳል።
በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ 1871 አንድ የሜዲካል ተማሪ ህይወቱን የለወጡትን 21 ቃላት ከአንድ መፅሀፍ ላይ አነበበ። ይሄው የሜዲካል ተማሪ እንዴት መኖር፣ በምን እስፔሻላይዝ ማድረግ በመጨረሻም የት መስራት እንዳለበት እየተጨነቀ ወራትን አሳልፎአል። በመጨረሻም ህይወቱን የቀየሩላትን 21 ቃላት ከአንድ መፅሀፍ ላይ አነበበ። ይህም ፅሁፍ እንዲህ ይላል።
Our main business is not to see what lies dimly at a distance, but to do what lies clearly at hand.
ይህም በአማርኛ ሲተረጎም
‘በሩቅ ያለው ላይ ከማተኮር በእጃችን ላይ ያለውን እድል እንመልከት’ የሚል ትርጉም ይይዛል።
ይህም የሚያመለክተው ባለፈው ታሪክ ከመፀፀትም ሆነ ስለወደፊቱ ከመጨነቅ ዛሬ ላይ ማተኮር እና መጠቀም እንዳለብን ነው።
ይህ የሕክምና ተማሪ ሰር ዊሊያም ኦስለር (Sir William Osler) ይባላል። ጆን ሆፕኪንግ ሆስፒታልን ከመሰረቱ 4 ፕሮፌሰሮች መካከል አንዱ ነው። የመጀመሪያውን የሬዚደንሲ ፕሮግራም የጀመረ እና የሕክምና ተማሪዎችን ለመጀመሪያ ጊዜ ከ መማሪያ ክፍል በተጨማሪ ከ ታማሚዎች በቀጥታ እንዲማሩ ያደረገ ሐኪም ነው።
እስኪ እርስዎ በአሁኑ ሰዐት የሚያስጨንቅዎትን ነገር ያስቡ። አብዛኛውን ጊዜ የሚያሳልፉት ስላለፈው ህይወትዎ በመፀፀት ነው ወይስ ስለሚመጣው ህይወትዎ በመጨነቅ? ስላለፈው ህይወትዎ መፀፀትም ሆነ ስለሚመጣው ህይወትዎ መጨነቅ ለእርስዎ ምን አስተዋጽኦ አለው? ከዚህ ሁሉ ወደ ፊት የሚፈልጉትን ህይወት ለመኖር የሚረዳዎትን እርምጃ ለምን አይጀምሩም?
መልሱን ለእናንተ ተውኩ።