10 አደገኛ የኩላሊት በሽታ ምልክቶች (10 SYMPOMES OF KIDNEY DISEASE)

ኩላሊት ደምን የሚያጣራ የሰውነት ክፍል ሲሆን በአንድ ቀን ውስጥ እስከ 200 ሊትር ደም በማጣራት በሰውነታችን ውስጥ ያሉትን እንደ ጨው እና ውሃን ጨምሮ ሌሎች ሰውነታችን ከሚፈልገው በላይ የሆኑ ንጥረ ነገሮችን እና መርዛማ ኬሚካሎች በሽንት መልክ እንዲወጣ ያደርጋል። በሰውነታችን ውስጥ ያሉትን ንጥረ ነገሮች ከመመጠን እና ኬሚካሎችን ከማጣራት ባሻገር ኩላሊት የደም ግፊትን ይቆጣጠራል እንዲሁም የቀይ የደም ህዋስ እንዲሰራ የሚያገለግል ኢሪትሮፖኢቲን የሚባል ኬሚካል እና አጥንትን የሚያጠነክር ቫይታሚን ዲ የሚባል ንጥረ ነገር እንዲሰራ ያደርጋል። በዚህ አጭር ፁሁፍ ስለ የኩላሊት በሽታ ምልክቶች እንዳስሳለን፤ መልካም ንባብ።

የኩላሊት በሽታ

የኩላሊት ህመም አይነቶች

በመጀመሪያ በኩላሊት ላይ የሚደርስ ጉዳት በሁለት ይከፈላል።

 1. አጣዳፊ (Acute Kidney Disease) እና
 2. የቆየ (Chronic Kidney Disease)

አጣዳፊ የኩላሉት በሽታ (Acute Kidney Disease) የሚባለው ከ 3 ወር ባነሰ ጊዜ በኩላሊት ላይ የሚደርስ ጉዳት ሲሆን የኩላሊት በሽታው ከ 3 ወር ከበለጠ የቆየ እንለዋለን። ሌላው ሁለቱን የኩላሊት በሽታዎች የሚለያያቸው የሚያሳዩት ምልክት ነው። ከስሙ መረዳት እንደምንችለው አጣዳፊ የኩላሊት በሽታ የተለዩ ምልክቶች ስላሉት በሽተኞቹ ቶሎ ወደ ሐኪም ቤት በመሔድ ተገቢውን ሕክምና ስለሚያገኙ የመዳን እድላቸው ከፍተኛ ነው።

የቆየ የኩላሊት በሽታ (Chronic Kidney Disease) ግን ብዙም ምልክቶች ሳያሳይ ለከፋ ችግር ሊያዳግት ይችላል። በሽተኞቹም የዲያሊሲስ ሕክምና ረዘም ላለ ጊዜ የመፈለግ እድላቸው ከፍተኛ ነው።

ይህን ካልን እስኪ የሁለቱንም ምልክቶች እንይ።

የኩላሊት በሽታ ምልክቶች

አጣዳፊ የኩላሊት በሽታ የሚያሳየው ምልክቶች ምን ምንድን ናቸው?

የኩላሊት ህመም ምልክቶች
የኩላሊት ህመም የሰውነት ማበጥን ያስከትላል
 • የሽንት መጠን ማነስ ፣ ወይም በጭራሽ አለመሽናት፡፡ ይህም ማለት በ 24 ሰዓት ውስጥ ያለን ሽንት ተለክቶ ከ 400 ሚሊ ሊትር ያነሰ ከሆነ። ይህም የሚያመለክተው ኩላሊት የማጣራት አቅሟን እንዳጣች ነው። ይህም በሰውነት ውስጥ ውኃ እንዲጠራቀም ምክንያት ይሆናል። ይህም ሁለተኛውን ምልክት እንዲፈጠር ያደርጋል። ይህም የሰውነት ማበጥ ነው።
 • የሰውነት ማበጥ በብዛት የሚከሰተው ጠዋት ጠዋት በፊት እና አይን አካባቢ ሲሆን እየቆየ ሲሄድ ደግሞ በሆድ እና በእግር ላይ እብጠት ሊታይ ይችላል።
 • ውኃው የተጠራቀመው በደረት አካባቢ ከሆነ የደረት ሕመም ወይም ግፊት እና የትንፋሽ እጥረት ሊኖር ያችላል።
 • ሌላው በሰውነት ውስጥ ያለው የውሃ መጠን በመጨመሩ ምክንያት ከፍተኛ የሆነ የደም ግፊት ሊኖር ይችላል። ከዚህም ጋር ተያይዞ የራስ ምታት እና የአይን ብዥታ ሊኖር ይችላል።
 • ከዚህ በተጨማሪ ደም የቀላቀለ፣ ቀይ ወይም ቡናማ የሆነ ሽንት ልናይ እንችላለን።ይህም ሽንትን የኮካ ኮላ ቀለም እንዲኖረው ያደርጋል። ይህም የኩላሊት መጎዳትን ያመላክታል።
 • በስደስተኛነት ደረጃ የሚጠቀሰው ምልክት ማስታወክ እና የምግብ ፍላጎት አለመኖር ሲሆን የዚህ ዋነኛ ምክንያቱ ዩሬሚያ የሚባል መርዛማ ኬሚካል በሰውነታችን ውስጥ ስለከማች ነው።
 • ሌላው ምልክት ደግሞ በቀላሉ የመድከም ስሜት ነው።
 • እንዲሁም ሽንት ከመጠን ያለፈ አረፋ ካለው በሽንት ውስጥ ፕሮቲን እንዳለ ሊያመላክት ይችላል። ጤነኛ ሰው ላይ በሽንቱ ውስጥ ከመጠን ያለፈ ፕሮቲን እንዲኖር አይጠበቅም፤ ኩላሊት አጣርቶ ወደ ደም ይመልሰዋል። ነገር ግን ኩላሊት ሲጎዳ በሽንት ውስጥ ፕሮቲን ሊገኝ ይችላል።

የቆየ የኩላሊት በሽታ የሚያሳየው ምልክቶች ምን ምንድን ናቸው?

ከላይ ለመግለፅ እንደተሞከረው የቆየ የኩላሊት በሽታ ይህ ነው የሚባል ምልክት ላያሳይ ይችላል። በዚህ ምክንያት አብዛኛውን ጊዜ ህመምተኞች ለመታከም ወደ ሐኪም ቤት በሚመጡበት እና የኩላሊት በሽታ እንዳለባቸው በሚያውቁበት ጊዜ ህመሙ መዳን የማይችልበት ደረጃ ሲሆን ይታያል። ለዚህም ነው ለዲያሊሲስ እና የኩላሊት ንቅለ ተከላ የሚያስፈልጋቸው የኩላሊት ሕመምተኞች በብዛት የምናየው።

እንደ አጠቃላይ ግን ከቆየ የኩላሊት በሽታ ጋር ተያይዘው የሚመጡ ምልክቶች የሚከተሉት ናቸው።

 • የደም ማነስ ምልክቶች ይህም ራስ ምታት፣ ማዞር፣ ጆሮ ላይ የሚጮህ ድምፅን ያጠቃልላል። ቀደም ሲል እንደገለፅነው ኩላሊት ኢሪትሮፖኢቲን የሚባል የቀይ የደም አይነት እንዲመረት የሚያደርግ ኬሚካል ያመርታል፤ ስለሆነም የቆየ የኩላሊት በሽታ ሲኖር ይህ ኬሚካል መመረቱ ስለሚቀንስ እና በሌሎች ተያያዝ ምክንያቶች አማካኝነት የደም ማነስ እንዲኖር ያደርጋል።
 • ሌላው ደግሞ ሶዲየም፤ ፎስፈረስን እና ቫይታሚን ዲን ጨምሮ የተለያዩ በደማችን ውስጥ የሚገኙ ንጥረ ነገሮች ሊዛቡ ይችላሉ። በዚህ ምክንያት የአጥንት በሽታ ሊከሰት ይችላል።
 • በሽታው እየባሰ ሲሄድ ደግሞ አእምሮ መሳት እና ከእንቅልፍ ጋር የተያያዙ ችግሮች ሊከሰቱ ይችላሉ።
 • በተጨማሪም በሰውነት ውስጥ የተከማቸው መርዛማ ኬሚካል ወደ ጭንቅላት ከደረሰ ንቃተ ህሊና መቃወስ ሊያጋጥም ይችላል።

ስለዚህም ከላይ የተጠቀሱት ምልክቶች ካለዎት ቶሎ ወደ ጤና ተቋም በመሔድ ተገቢውን ሕክምና ማግኘት ይኖርብዎታል። እንዲሁም ሕክምናውን እና መድኃኒቱን በሚገባ መውሰድ እና ሐኪምዎ የሚያዝልዎትን ነገሮች በአግባቡ መተግበር ይኖርብዎታል። በተጨማሪም በቀጠርዎ ቀን እና ሰዐት በመገኘት አስፈላጊውን ክትትል ማድረግ ያስፈልጋል።

በቀጣይ አጣዳፊ እና የቆየ የኩላሊት በሽታ የሚያስከትሉ ነገሮችን እናያለን። ቸር ሰንብቱ።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top