ሁላችንም እንደምናውቀው ኮቪድ 19 ( ኮሮና ) ወደ ሀገራችን ከገባ ከ አንድ አመት ከ 6 ወር በላይ ሆኖታል። ይህ በሽታ እስካሁን ድረስ በአለም ላይ 227 ሚሊዮን ገደማ የሚሆኑ ሰዎች በበሽታው የተጠቁ ሲሆን ከነሱ ውስጥ 4.6 ሚሊዮን የሚሆኑት ደግሞ ህይወታቸውን አተዋል። በተመሳሳይ በሀገራችን በኢትዮጵያ ከ 300 ሺህ በላይ የሚሆኑ ሰዎች በበሽታው የተጠቁ ሲሆን ከዚህ ውስጥ ከ 5 ሺህ በላይ የሆኑት ህይወታቸው አልፏል።
ይህን አስከፊ በሽታ ለመከላከል ማስክ እና ሳኒታይዘር ከመጠቀም እንዲሁም የአንድ ሜትር ርቀት ከመጠበቅ ባሻገር ክትባቱን በመውሰድ ራሳችንን መጠበቅ እንችላለን። እስካሁን የአለማችን 30.7 በመቶ የሚሆነው ህዝብ ሙሉ በሙሉ ክትባቱን የወሰደ ሲሆን ወደ ኢትዮጵያ ስንመጣ ግን በክትባት እጥረት እንዲሁም በቂ መረጃ ባለማግኘት ምክንያት 0.5% የሚሆነው ህዝብ ብቻ ነው ሙሉ ክትባቱን የወሰደው። ስለዚህም በዚህ ፁሁፍ በ ኮቪድ 19 (ኮሮና) ክትባት ዙሪያ አስፈላጊ የሚባሉትን ነጥቦች እናነሳለን።
የ ኮቪድ 19 ክትባቶች፤ ሰውነታችን በበሽታው እንዳይጠቃ የመከላከል ዐቅሙን እንዲፈጥርና ኮቪድ 19 ን ለሚያስከትለው ቫይረስ የበሽታ መከላከያ እንዲያዳብር ይረዱታል፡፡
የ ኮቪድ 19 ክትባት አይነቶች
በአሁኑ ጊዜ በ WHO የተፈቀዱ 7 የ ኮቪድ 19 (ኮሮና) ክትባት አይነቶች ሲኖሩ ከነሱ ውስጥ አምስቱን እናያለን።
PFIZER BioN TecH (ፋይዘር ባዮኤን ቴክ ክትባት)
ይህ የ ኮቪድ 19 ( ኮሮና ) ክትባት የተሰራው አሜሪካ እና ጀርመን ሃገር ሲሆን የመከላከል አቅሙ ከ 90 እስከ 94% የሚደርስ ነው። ይህን ክትባት ዕድሜያቸው 12 ዓመት እና ከዚያ በላይ የሆኑ ሰዎች መከተብ የሚችሉ ሲሆን በሶስት ሳምንታት ልዩነት ሁለት ጊዜ ክትባቱን መወጋት ይኖርብናል።
MODERNA (ሞደርና ክትባት)
ይህ የ ኮቪድ 19 ( ኮሮና ) ክትባት የተሰራው አሜሪካ ሃገር ሲሆን የመከላከል አቅሙ ከ 90 እስከ 94% የሚደርስ ነው። ይህም ክትባት ዕድሜያቸው 18 ዓመት እና ከዚያ በላይ የሆኑ ሰዎች መከተብ የሚችሉ ሲሆን በአራት ሳምንታት ልዩነት ሁለት ጊዜ ክትባቱን መወጋት ይኖርብናል።
JOHNSON AND JOHNSON (ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን ክትባት)
ይህ የ ኮቪድ 19 ( ኮሮና ) ክትባት የተሰራው አሜሪካ እና ቤልጂየም ሃገር ሲሆን የመከላከል አቅሙ ከ 70 እስከ 85% ይደርሳል። ክትባቱን መወጋት የሚጠበቅብን አንድ ጊዜ ብቻ ሲሆን ዕድሜያቸው 18 ዓመት እና ከዚያ በላይ የሆኑ ሰዎች መውሰድ ይችላል።
ASTRAZENECA (አስትራዜኒካ ክትባት)
ይህ የ ኮቪድ 19 ( ኮሮና ) ክትባት የተሰራው ኢንግላንድ እና እስዊድን ሃገር ሲሆን የመከላከል አቅሙ ከ 70 እስከ 90% የሚደርስ ሲሆን ከሁለት እስከ ሶስት ወራት ልዩነት ሁለት ጊዜ ክትባቱን መወጋት ይኖርብናል።
Sinopharm (ሲኖራርም)
ይህ የ ኮቪድ 19 (ኮሮና) ክትባት ኮቪድን የመከላከል አቅሙ 79% ሲሆን ይህም ክትባት ዕድሜያቸው 18 ዓመት እና ከዚያ በላይ የሆኑ ሰዎች መከተብ የሚችሉ ይችላሉ። ክትባቱ እንዲሰራ በአራት ሳምንታት ልዩነት ሁለት ጊዜ ክትባቱን መውሰድ ይኖርብናል።
ክትባቱ በምን ያህል ጊዜ ይሰራል? ለምንስ ያህል ጊዜ ይቆያል?
ሁሉም ክትባቶች የመጨረሻው ዶዝ ከተሰጠ ከ 2 ሳምንት በኃላ መስራት ይጀምራሉ። እንዱሁም በመጀመሪያዎቹ 6 ወራት ውስጥ በሽታውን የመከላከል እንዲሁም ከባዱ የበሽታው ምልክቶችን በመቀነስ በኮቪድ ምክንያት የሚከሰተውን የሞት መጠን ይቀንሳሉ።
ከተከተብኩ በኃላ ምን ማድረግ አለብኝ?
- ከተከተቡ በኃላ ቢያንስ ለ 15 ደቂቃ ያህል እዛው መቆየት
ይህም የሚጠቅመው የክትባቱ አላርጂክ የሆኑ ሰዎችን ለመለየት እና የሕክምና እርዳታ ለማድረግ ነው። ስለዚህ ማሳከክ፣ መቅላት የመሳሰሉ የአላርጂክ ምልክቶች ካዩ ወዲያው ለጤና ባለሙያዎች መናገርዎን አይርሱ።
- ቀጣይ ለሁለተኛው ክትባት መቼ እንደሚመጡ መጠየቅ እና ፅፎ መያዝ
- ብዙውን ጊዜ ክትባቱን የተወጉ ሰዎች ቀላል የሚባሉ የጎንዮሽ ጉዳቶች ሲያሳዩ ይስተዋላሉ። ለምሳሌ
- ክትባቱን የተወጉበት ቦታ ላይ የህመም ስሜት
- ቀለል ያለ ትኩሳት
- ብርድ ብርድ ማለት
- ድካም
- ራስ ምታት
- የጡንቻ እና የመገጣጠሚያ ህመም
ከላይ የተጠቀሱት የጎንዮሽ ጉዳቶች ከ 10 ሰዎች ውስጥ አንዱ ላይ የሚታዩ ሲሆኑ እረፍት በማድረግ እንዲሁም የራስ ምታቱን ለመቀነስ እንደ ፓራስታሞል ያሉ መድኃኒቶችን መጠቀም ያስፈልጋል።
እንደ ደም መርጋት ያሉ ከኮቪድ ክትባት ጋር የተያያዙ የጎንዮሽ ጉዳቶች ክትባቱን ከወሰዱ 100,000 ሰዎች መካከል አንድ ሰው ላይ ብቻ የሚታዩ ስለሆኑ ክትባቱን ላለመውሰድ እንደምክንያት መቅረብ የለባቸውም።
በአሁኑ ጊዜ በመሠራት ላይ ያሉት ወይም ተቀባይነት ያገኙ የኮቪድ-19 ክትባቶች አዳዲስ የቫይረሱን ዝርያዎች ለመከላከል ቢያንስ የተወሰነ ጥበቃ እንደሚያደርጉ ይታወቃል፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ክትባቶች ሰዎች የተለያዩ ፀረ እንግዳ አካላትንና ሕዋስን የሚያጠቃልል ሰፊ በሽታ የመከላከል ዐቅም እንዲኖራቸው ያደርጋሉ። የበለጠ ቫይረሱ እንዳይስፋፋ እና ዝርያዎቹን እንዳያበዛ እጅግ የላቀ ጥንቃቄ እና ክትባቱን በተገኘነው አጋጣሚ መውሰድ ብቸኛው መፍትሔ ነው።
- በመጨረሻም ከተከተቡ በኃላም ቢሆን ጥንቃቄ አይለይዎት።
ለበለጠ መረጃ ቪዲዮውን ይመልከቱ።
የቱን የኮቪድ 19 ክትባት ልውሰድ ብለው ጠይቀው ያውቃሉ? እንግዲያውስ ቀጣዩን ቪዲዮ ይመልከቱ።