ኩላሊት በሰውነታችን ውስጥ ያሉ ንጥረ ነገሮች መጠናቸውን እንዲጠብቁ እንዲሁም ጎጂ ኬሚካሎች ከሰውነታችን ተጣርቶ እንዲወጣ የሚያደርግ የሰውነት ክፍል ነው። በመሆኑም ይህ በጣም አስፈላጊ የሆነውን የሰውነታችንን ክፍል ጤንነት ለመጠበቅ የሚረዱ የተለያዩ መንገዶችን በመተግበር የኩላሊት በሽታን መከላከል እንችላለን። በዚህ ትምህርታዊ ፁሁፍ ላይ ስለ 9 የኩላሊት በሽታ መከላከያ መንገዶች እናያለን፤ መልካም ንባብ።
ተያያዥ ፁሁፎች
በቂ ውሃ መጠጣት
ኩላሊት ስራዋን በትክክል እንድትሰራ በቂ የሆነ ደም ያስፈልጋታል። ስለዚህም ማንኛውም የደምን መጠን የሚቀንሱ ነገሮች ኩላሊት ላይ ከባድ አደጋ ሊጥሉ ይችላሉ።
በመሆኑም በየቀኑ በአማካኝ ከ 1.5 እስከ 2 ሊትር ውኃ በመጠጣት የኩላሊትን ጤንነት መጠበቅ ይችላል። በተመሳሳይ እንደ ተቅማጥ እና ተውከት ያሉ የደም መጠንን የሚቀንሱ ምልክቶችን ካየን በአፋጣኝ ወደ ጤና ተቋም በመሔድ ተገቢውን ምርመራ እና ሕክምና ማግኘት እንዲሁም የወጣውን ፈሳሽ ለመተካት ኦአርኤስ መጠቀም ያስፈልጋል።
ከፍተኛ የደም መፍሰስ ካጋጠመ ወዲያው መተካት
የመኪናም ሆነ ማንኛውም አደጋ ከተፈጠረ የሚታይም ሆነ የማይታይ የደም መፍሰስ ሊኖር ስለሚችል አደጋ የደረሰበትን ግለሰብ በፍጥነት ወደ ሐኪም ቤት መውሰድ ያስፈልጋል።
የእርግዝና ጊዜ ክትትልን በአግባቡ መከታተል እንዲሁም በጤና ተቋም ውስጥ መውለድ
የእርግዝና ክትትልን በአግባቡ መከታተል እና በጤና ጣቢያ መውለድ በጣም አስፈላጊ ነው። ምክንያቱም ከእርግዝና እና ከወሊድ ጋር ተያይዞ የሚመጣ የደም መፍሰስ ለኩላሊት በሽታ ብሎም ለሞት ሊዳርግ ይችላል። ስለሆነም ቶሎ ሕክምና የሚሰጡ የጤና ባለሙያዎች እንዲሁም ከደም መፍሰስ ጋር በተያያዘ እናቲቱ ተተኪ ፈሳሽ ሆነ ደም ቢያስፈልጋት ቶሎ ልታገኝበት የምትችልበት ቦታ ላይ መውለድ አለባት። ምክንያቱም የደም መፍሰስ እንኳ ቢኖር ኩላሊት እና አዕምሮ ከመጎዳቱ በፊት መታከም ይችላል ማለት ነው።
መድኃኒቶችን ከመውሰዳችን በፊት የጤና ባለሙያን ማማከር
መድኃኒቶችን ከመውሰዳችን በፊት የጤና ባለሙያን ማማከር ያስፈልጋል። ምክንያቱም አንዳንድ መድኃኒቶች ኩላሊትን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ሊጎዱ ይችላሉ።
ለምሳሌ
- ሽንት የሚያሸኑ መድኃኒቶች
- እንደ ዳይክሎፌናክ፤ አይቡብሩፌን እና አስፕሪን ያሉ መድኃኒቶች የህመም ማስታገኛ መድኃኒቶች
- ለካንሰር ሕክምና የሚሰጡ የኬሞቴራፒ ሕክምናዎች እንዲሁም
- አንዳንድ የ ፀረ ባክቴሪያ መድኃኒቶች ከብዙ በጥቂቱ ይጠቀሳሉ።
የኩላሊት ኢንፌክሽን ምልክቶችን ካዩ ቶሎ መታከም
እንደ የጎን ህመም፣ ትኩሳት፣ የሽንት ቶሎ ቶሎ መምጣት እና ማጣደፍ፣ ሲሽኑ የማቃጠል ስሜት እንዲሁም የማስመለስ እና የማቅለሽለሽ ስሜት ካለ የኩላሊት ኢንፊክሽን ሊሆን ስለሚችል ቶሎ ወደ ጤና ተቋም በመሔድ መታከም ያስፈልጋል።
የኩላሊት ጠጠር ምልክቶችን ካዩ ቶሎ መታከም
በተመሳሳይ የጎን እና የጀርባ ህመም እና ደም የቀላቀለ ሽንት ካለዎ የኩላሊት ጠጠር ሊሆን ስለሚችል ቶሎ መታከም ያስፈልጋል።
የስኳር በሽታን መከላከል ወይም መቆጣጠር
የስኳር በሽታን መከላከል እንዲሁም የስኳር በሽታ ተጠቂ ከሆኑ ደግሞ መድኃኒቱን በአግባቡ በመውሰድ፣ አመጋገብን በማስተካከል እንዲሁም የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በማድረግ የስኳር መጠናችንን መቆጣጠር አስፈላጊ ነው። አብዛኛውን ጊዜ በስኳር በሽታ የተጠቁ ሰዎች ሳያውቁት ኩላሊታቸው በከፍተኛ ደረጃ ተጎድቶ ሊገኝ ስለሚችሉ በስርዐት ክትትል እንዲያደርጉ ይመከራል።
የደም ግፊትን መከላከል ወይም መቆጣጠር
የደም ግፊት ተጠቂ ከሆኑ ደግሞ ስኳር በመቀነስ፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በማድረግ እንዲሁም ክብደት በመቀነስ ኩላሊት ላይ የሚደርሰውን ጫና መቀነስ ይችላል።
የ መ ህጎችን መተግበር
የኤች አይ ቪን በሽታም ሆነ የጉበት በሽታ የሚያስከትሉ ቫይረሶች ኪላሊት ላይ ጉዳት ስለሚያስከትሉ የ መ ህጎችን በመተግበር (ይህም መታቀብ፣ መወሰን ወይም ኮንዶም መጠቀም ሲሆኑ) እነዚህን ህጎች በመተግበር ራሳችንን መከላከል ይመከራል።
የኩላሊት በሽታ ምልክቶችን ካዩ በአስቸኳይ ወደ ጤና ጣቢያ በመሄድ ሕክምና መጀመር
- እንደ የሽንት መጠን ማነስ ፣ ወይም በጭራሽ አለመሽናት፡፡
- የሰውነት ማበጥ
- ደም የቀላቀለ የኮካ ኮላ ቀለም ያለው ሽንት
- ማቅለሽለሽ እና የምግብ ፍላጎት ማጣት
- ድካም የመሳሰሉትን የአጣዳፊ የኩላሊት በሽታ ምልክቶችን ካዩ በፍጥነት ወደ ጤና ተቋም በመሄድ ተገቢውን ምርመራ እና ህክምና ማግኘት ያስፈልጋል። ይህም ኩላሊት ሙሉ በሙሉ ሳይጎዳ ኩላሉትን በማከም የቆየ የኩላሊት በሽታ እንዳይከሰት መከላከል ይችላል።
ለበለጠ ማብራሪያ ቀጣዩን ቪዲዮ ይመልከቱ።